የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማዳረስ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ በክልሉ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ለሚገኘው ማኅበረሰብ ክፍሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማዳረስ የሚያግዝ ድጋፍ አድርጓል።
ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረገው ድጋፍ ላይ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።
የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ውሃ መቅጃ እቃዎች፤ ከ 3 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ 20 ሺህ ሊትር የሚይዙ ታንከሮችን ጨምሮ በመጀመሪያ ዙር 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት ድጋፍ መደረጉን የቢሮው ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ተቋሙ ከተለያዩ የመጠጥ ውሃ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ውሃ ቀድተው የማቅረብ አገልግሎት የሚሰጡ 4 ቦቲዎችንና የጥገና ሥራ የሚሠሩ ቡድኖችን ማሠማራት መቻሉንም አመልክተዋል።
በአማራ ክልል ድርቁ በዘጠኝ ዞኖች በ43 ወረዳዎች የተከሰተ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ በተለይም በሰሜን ጎንደርና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ጉዳቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ትኩረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።
በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚኖረው ማኅበረሰብ ከሚደርሱበት ሰብአዊ ቀውሶች ውስጥ የውሃ አቅርቦት እጥረት አንዱ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው ለሰውና ለእንስሳት ንጹህ ውሃ በማቅረብ በሰውና በእንስሳት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመግታት ተቋሙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ረጂ ድርጅቶች፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በሀገር ውስጥም በውጭም የሚገኘው ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተቻለው ሁሉ እንዲረባረብም ኃላፊው ጠይቀዋል።
በደሳለኝ ቢራራ