አርሶ አደሩን ከልማዳዊ የግብርና አሰራር ልናወጣው ይገባል አሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉን አርሶ አደር የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን እና ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም በማድረግ ከልማዳዊ የግብርና አሰራር ልናወጣው ይገባል ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ የተፋሰስ ልማትና የበልግ አዝመራ ማስጀመሪያ ንቅናቄ መድረክ በወላይታ ሶዶ እየተካሄደ ነው።
አቶ ጥላሁን ከበደ በወቅቱ እንዳሉት÷ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የግብርና ዘርፍን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
“አመራሩና የሚደግፈው ባለሙያ አርሶ አደሩን ከተለመደው የአስተራረስ ዘዴ በማውጣት በኩታ ገጠም እንዲያለማና በቴክኖሎጂ በማገዝ በእጁ ያለውን ሀብት እንዲጠቀምበት ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
“ግብርና የብልፅግናን ትልም ለማሳካት ከያዝናቸው መንገዶች ዋንኛው ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ግብርናን ማዘመን የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በቀዳሚነት የተያዙ ዘርፎች የአምራች፣ የቱሪዝም፣ የማዕድንና የቴክኖሎጂ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በክልሉ በቂ መሬት፣ ውሃ፣ የሰው ሃይልና ምቹ የአየር ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ “አቅማችንን በመገንባት ብልፅግናን እውን እናደርጋለን” ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው÷ ቢሮው በግብርና ዘርፍ የታለመውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።