Fana: At a Speed of Life!

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በተከሰሰባቸው ተደራራቢ ክሶች እንዲከላከል ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ባልቻ በቅጽል ስሙ (ልጅ ያሬድ) በተከሰሰባቸው ተደራራቢ ክሶች ተጠቃሎ እንዲከላከል ብይን ተሰጠ።

ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ህገመንግስታዊና በህገመንግስት ስርዓቱ ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ላይ ሶስት ክሶችን አቅርቦበት ነበር።

ከቀረቡበት ክሶች መካከል በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም ማጉደፍ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ተደራራቢ ክሶች ይገኙበታል።

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም የቀረበበት ክስ እንዲሻሻል የክስ መቃወሚያውን በጽሁፍ ያቀረበ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ በኩል ክሱ ሊሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ እንደሌለ ተጠቅሶ መልስ ተሰቷል።

ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ ተከሳሹ ያቀረበው የክስ መቃወሚያ ጥያቄ የህግ አግባብነት የለውም በማለት ውድቅ አድርጎታል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን በመጥቀስ የዕምነት ክህደት ቃሉን በመስጠቱ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማምረጃውን አቅርቧል።

የቀረበውን ማስረጃ የመረመረው ችሎቱ ተከሳሹ የቀረቡበት ሶስት ክሶች ተጠቃለው በአዋጅ ቁጥር 1185/2012 አንቀጽ 4 እና 7 መሰረት እንዲከላከል ብይን ተሰጥቷል።

ሶስቱም ክስ በአንድ እንዲጠቃለል የታዘዘው የወንጀል ድርጊቱ በሀሳብ፣ በጊዜና በቦታ ተመሳሳይ መሆኑን በምክንያትነት ተጠቅሶ ነው።

ተከሳሹ የመከላከያ ማስረጃ አለኝ ማለቱን ተከትሎ መከላከያ ማስረጃውን ለመጠባበቅ ፍርድ ቤቱ ለጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዕምነት ተከታይ የሆኑ ምዕመናንን እና የማህበረሰቡን ክብርና ስነልቦናን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ እንዳይሰራጭ ትዕዛዝ መስጠቱ ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡ (FBC (Fana Broadcasting Corporate S.C.)
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.