አምባሳደር ምስጋኑ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ልዑካን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ልዑካን ጋር ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ ትናንት በተጀመረው 19ኛው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ (ናም) ሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ጉባዔው “ይበልጥ መተባበር ለጋራ ዓለም አቀፍ ተፅእኖ” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ነው እየተወያየ የሚገኘው።
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የጸጥታ፣ የኢኮኖሚ እና የህብረተሰብ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ አንኳር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተደረገ ምክክር የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ሃሳባቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
የሚኒስትሮች ስብሰባ ከፈረንጆቹ ጥር 14 እስከ 15 የተካሄደውን የናም ጉባዔ ተከትሎ የተደረገ ሲሆን ፥ በሚቀጥለው የናም ጉባዔ ላይም ለውይይቱ መሰረት የሚጥሉ አንዳንድ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
አምባሳደር ምስጋኑ ከዚህ ጎን ለጎንም ከተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ልዑካን ቡድን ጋር በተናጠል መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡