የጥምቀት በዓል በደመቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊወጣ ይገባል – ከንቲባ አዳነች
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጥምቀት በዓል ደማቅና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊወጣ እንደሚገባ አስገነዘቡ፡፡
ከንቲባ አዳነች የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ባማረና በደመቀ መልኩ እንዲከበር ዛሬ የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው፤ ለጥምቀት ወደ ከተማችን የሚመጡና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን የሚስብ የቱሪስት ስበትና እና በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ የሀገራችን ሀገራዊ ቅርስ በመሆኑ ደማቅና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅዖ ሊወጣ ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል::
አክለውም በዓሉ የሰላምና የፍቅር በመሆኑ በሰላም፣ በመከባባርና መደጋገፍ እንድናከብረው ጥሪዬን ላስተላለፍ እወዳለሁ ብለዋል፡፡