በጎንደር ለጥምቀት በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ ለሚከበረው የከተራ እና የጥምቀት በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የጎንደር ከተማ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩ አቡሃይ በሰጡት መግለጫ ÷ በዓሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲከበር ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይም በዓሉን በድምቀት እና በሰላማዊ ሁኔታ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ነው የገለጹት፡፡
በበዓሉ ለመታደም እንግዶች እየገቡ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ÷ ወደ ጎንደር በቀን በአማካይ 11 በረራ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡
በከተማው የሚገኙ ሆቴሎች ለእንግዶች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡና የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ መግባባትላይ መደረሱንም ነው የተናገሩት፡፡
ከ130 ሄክታር በላይ መሬት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች መዘጋጀቱን አቶ ባዩ አቡሃይ ገልጸዋል።
በዓሉ በሰላም እንዲከበር በቂ የፀጥታ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ÷ የከተማዋ ወጣቶችም የተለመደ ቀና ትብብራቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተቀዳሚ ም/ከንቲባ ባዩ አቡሃይ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በምናለ አየነው