ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ በጋራ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴሩ ከፈረንሳይ ፓርላማ የመከላከያ ጉዳዮች ኮሚቴ አባላት ጋር በጋራ ለመስራት በሚያስችል መልኩ ውይይት መደረጉን ውይይቱን የተካፈሉት የመከላከያ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል ወርቁ ከበደ ገልፀዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት÷ በፈረንሳይና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት መሆኑን ብርጋዲየር ጄኔራል ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላት አብርሃም በላይ (ዶ/ር) መግለፃቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አብርሀም በላይ (ዶ/ር) አባላቱ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ባደረጉት ውይይት ደስተኛ መሆናቸውንና የኢትዮጵያ መከላከያ ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል ተብሏል፡፡
የፈረንሳይ ፓርላማ የመከላከያ ጉዳዮች ኮሚቴ አባላትን የወከሉት ቶማስ ጋሲሎይድ÷ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት በቀጣናዊ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብሮች ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይል ግንባታና ድጋፍ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን ተጠቅሷል፡፡