Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ የስዊዘርላንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ጠየቁ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የስዊዘርላንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ጠየቁ፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ከስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናሲዮ ካሲስ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በዳቮስ ያካሄዱት ውይይት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችላቸው ጉዳዮችን እና በባለብዙ ወገን መድረኮች በሚኖራቸው ትብብር ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል።

አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ እንዳሉት÷ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ መስክ የሁለቱን ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ምቹ ጊዜ እንደሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረች ስላለው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲም ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፥ ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ እንደ ቴሌኮም ያሉ ክፍለ ኢኮኖሚዎችን ክፍት ያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ የፋይናንስ ዘርፉን በተመሳሳይ ክፍት እንሚሆንም መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የስዊዘርላንድ ኩባንያዎች በተጠቀሱት እና ሌሎች ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት በሆኑ መስኮች ተሳታፊ በመሆን እያደገ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ፥ ስዊዘርላንድ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባልነቷ ለምታንፀባርቀው ሚዛናዊ አቋም ምስጋና አቅርበው ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የስዊዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናስዮ ካሲስ በበኩላቸው÷ በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።

በቀጣይ መጋቢት ወር በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዳቸውን ሚኒስትሩ ጨምረው የገለፁ ሲሆን÷ ጉብኝቱ የሀገራቱን ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ለማስፋት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.