50 የእጅ ቦምብ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ እንዲከላከሉ ተበየነ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 50 የእጅ ቦምብ ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊያቀብሉ ነበር ተብለው የተከሰሱ ሶስት ግለሰቦች እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገመንግስትና በህገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ብይን ሰጠ።
1ኛ አማንኤል ግርማ፣ 2ኛ አብዶ መላኩ እና 3ኛ ደጋጋ ፈቀደ የተባሉ ተከሳሾች ላይ የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 የወጣዉን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 27 ንዑስ ቁጥር 1 እና አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ና ለ እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 9/ሐ ስር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በክሱ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሾቹ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዉሳኔ ቁጥር 10/2013 መሰረት ሽብርተኛ ብሎ የተሰየመዉን የሽብር ቡድን በቀጥታ እየረዱ መሆኑን እያወቁ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀሰዉ የሸኔ ሽብር ቡድን ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለቡድኑ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እና ድጋፍ በማድረግ ላይ ተሰማርተዉ የሚሰሩ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ ጠቅሷል።
በተለይም 1ኛ ተከሳሽ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ከሚንቀሳቀስ የሸኔ ሽብር ቡድን አባል ከሆነዉ ነጋሳ ምሬሳ (አዱኛ ተስፋዬ) ከተባለ ሰዉ ጋር በመገናኘት በነሃሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም የቡድኑ አባል ነው የተባለው ግለሰብ ካሳሁን በተባለ ሰዉ አማካኝነት ከአፋር ክልል አዋሽ ከተማ ቦምብ ይዞ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ እና ተቀብለህ ”እኔ በምልከዉ ሌላ ሰዉ ትልክልኛለህ ” በማለት እንደተነገረው ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
ተከሳሽም በጉዳዩ በመስማማት ጓደኛዉ ለሆነው ለ2ኛ ተከሳሽ ጉዳዩን በማሳወቅና ቦምቡን አብረው ሄደው ተቀብው ለማምጣት በመስማማት በነጋታው ማለትም በነሃሴ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በአ/አ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ቦታዉ ጋርመንት ወደሚባል ቦታ በመሄድ ከቀኑ 11፡30 አካባቢ 50 (ሃምሳ) ኤፍ ዋን (F1) የእጅ ቦምብ ከስምንት የቦምብ ፊዉዝ ጋር ማንነቱ ለጊዜዉ ካልተለየ ግልሰብ በመረከብ ወደ 2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት በመዉሰድ ደብቀዉ ማስቀመጣቸው በክሱ ተዘርዝሯል።
በነሃሴ 7 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ 2ኛ ተከሳሽ ባለቤቱና እናቱ ወደ ቤት እየመጡ በመሆኑ ”ቦምቡን አዉጥተን ሌላ ቦታ ማስወቀመጥ አለብን” በማለት ለ1ኛ ተከሳሽ ከገለጸ በኋላ 1ኛ ተከሳሽም ሃሳቡን በመቀበል ጉዳዩን ጓደኛዉ ለሆነ ለ3ኛ ተከሳሽ በማሳወቅ 3ቱም ተከሳሾች በሃሳቡ ተስማምተው ቦምቡን ከ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ወደ 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመውሰድ አንድ ላይ በጋራ በመሆን ወደ ከ2ኛ ተከሳሽ ቤት መሄዳቸው በክሱ ተገልጿል።
በዚህ መልኩ ቦምቡን ከ2ኛ ተከሳሽ ቤት አዉጥተዉ 3ኛ ተከሳሽ ቤት ለመደበቅና ለሸኔ ሽብር ቡድን አባል ለሆነ ግለሰብ ለማቀበል በማሰብ ሲንቀሳቀሱ በፖሊስ በተደረገባቸዉ ክትትል በቀኑ 9፡00 ሰዓት አካባቢ 3ቱም ተከሳሾች በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ ወረዳ 14 ልዩ ስሙ ሰፈራ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ በሚገኝ የ2ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ከ50 ኤፍ ዋን (F1) የእጅ ቦምብ እና ከ8 የቦምብ ፊዉዝ ጋር እጅ ከፍንጅ የተያዙ መሆኑን በመጥቀስ የሽብርተኛ ድርጅት የመርዳት ሙከራ ወንጀል ክስ ዐቃቤ ሕግ አቅርቦባቸዋል እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አያይዞ አቅርቦና ለተከሳሾች እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ተከሳሾቹ ክሱ እንዲሻሻልላቸው የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱም የተከሳሾቹን የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ ሕግ መልስን መርምሮ ክሱ መሻሻል የሚችልበት የህግ አግባብ የለም ሲል የቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።
ከዚህም በኋላ ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምንም ሲሉ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ዐቃቤ ሕግም ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን መርምሮ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ድርጊት መፈጸሙን በማረጋገጥ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።
የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለጥር 27 እና 28 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ