Fana: At a Speed of Life!

“ዓድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ፎረም ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) “ዓድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የንቅናቄ ፎረም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዛሬ መጀመሩን የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል።

በፎረሙ ዋና ዓላማ ዙሪያ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)÷አባቶቻችን በዓድዋ ጦርነት ላይ ያስመዘገቡት ድል ዜጎች በአንድነትና በአብሮነት ለጋራ ዓላማ በጋራ ከቆሙ መፍታት የማይቻል ችግር አለመኖሩን የሚያስተምር ነው ብለዋል።

ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ከሚገባቸው ባለድርሻ አካላት መካከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በዚህም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር “ዓድዋን ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ቃል እስከ የካቲት 21 ቀን2016ዓ.ም የሚቆይ የንቅናቄ ፎረም በይፋ መጀመሩን አስረድተዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ሀገራዊ ማንነትንና እሴቶችን የተመለከቱና በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ያተኮሩ ምክክሮች እንደሚካሄዱ  የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው÷ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጠንካራ ሀገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት  እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።

ንቅናቄው ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እና በተለያዩ አካላት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰከነ መንፈስ ለመፍታት የሚቻልበትን አቅጣጫ ያመላክታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.