በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ 12 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በአቶ አባተ አበበ የግድያ ወንጀል የተጠረጠረው ተስፋዬ ሆርዶፋ ላይ 12 ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ለፖሊስ ፈቀደ።
ተጠርጣሪ ተስፋዬ ሆርዶፋ በታህሳስ 7 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ ከምሽቱ 4:00 ላይ አባተ አበበ የተባለ ግለሰብን በ3 ጥይት በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል ተብሎ በፖሊስ ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።
ዛሬ ለ3 ኛ ጊዜ ከጠበቃው ጋር ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ በታየው ተጠርጣሪ ላይ ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ ከዚህ በፊት ለመርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የ14 ቀናት ጊዜ ውስጥ የተሰሩ የምርመራ ውጤቶችን ተመልክቷል።
በዚህም ፖሊስ በተሰጠው ጊዜ የ16 ሰው ምስክር ቃል መቀበሉን፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት ማስመጣቱን፣ ከሟች የተወሰደ ንብረትን የማስመለስ ስራ መስራቱን፣ የግድያ ወንጀል ተፈጽሞበታል ተብሎ የተጠረጠረውን የጦር መሳሪያ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን እና የቅድመ ምርመራ መዝገብ ማስከፈቱን ገልጿል።
ፖሊስ የአስከሬን የምርመራ ውጤት ላይ ማብራሪያ መጠየቅ፣ የተደረጉ የስልክ ልውውጦችን ከሚመለከተው ተቋም ማቅረብ እና ቀሪ ምስክሮችን አፈላልጎ ቃል የመቀበል ስራዎች እንደሚቀሩት ጠቅሷል።
በተጨማሪም መርማሪ ፖሊስ በምስክሮች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰ መሆኑን ጠቅሶ፤ ተጠርጣሪው ካለው ኢኮኖሚያዊ አቅም አኳያ ቢወጣ ምስክር ሊያሸሽብኝ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው በመጥቀስ የምርመራ ስራውን አጠናቆ ለዐቃቤ ሕግ ለማስወሰን ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።
በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል ደግሞ የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ አጠያየቅ ነጥቦችን በሚመለከት መቃወሚያዎች ተነስተዋል።
ከዚህም ከተነሱ መቃወሚያዎች መካከል ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ባልተባለበት ጉዳይ ላይ መርማሪ ፖሊስ አስቀድሞ የተጠርጣሪውን ንፁህ ሆኖ የመገመት ህገመንግስታዊ መብት በጣሰ መንገድ በመደምደም ግለሰቡን ወንጀል እንደፈጸመ አድርጎ ለጊዜ ቀጠሮ ማቅረቡ ተገቢነት የለውም የሚል መከራከሪያ ነጥብ ይገኝበታል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ሌላ የግድያ ሙከራ የፈጸመበት የጦር መሳሪያን የማግኘት ስራ ተሰርቷል ብሎ የተጠርጣሪውን የቀደመ የወንጀል ታሪክ መጥቀሱ የስነስርዓት ህጉን የተከተለ አይደለም በሚል በተጠርጣሪ ጠበቃ በኩል ክርክር ተደርጓል።
የተጠርጣሪ ጠበቃ ግለሰቡ ከመንግስት ተቋም የሚመጡ ማስረጃዎች የማጥፋት አቅም እንደሌለው በመጥቀስ ከዚህ በፊት ለፖሊስ የተሰጡ የተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ በቂ ነው በማለት ተከራክረዋል።
በተለጨማሪም ”በሚዲያዎች በኩል የተጠርጣሪውን ፎቶ በመለጠፍ ግለሰቡ እንደወንጀለኛ እንዲቆጠር እየተደረገ ነው” የሚል አቤቱታ በጠበቃ በኩል ቀርቦ ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ትዛዝ እንዲሰጥበት ተጠይቋል።
በተጨማሪም ፍትህን የማገዝ ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በሟች ቤተሰብ በኩል ተገቢ ያልሆኑ ቃላቶች ተሰንዝሮብኛል በማለት ጠበቃው አመልክተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ በወንጀል ስነስርዓት ህጉ መሰረት በጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የተጠርጣሪው የቀደመ የወንጀል ታሪክ ተጠቅሶ በችሎት ሊቀርብ እንደማይገባ ለፖሊስ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።
ሚዲያዎችን በሚመለከት የቀረበው አቤቱታ ህጋዊ መሰረት ያለው ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም።
ይሁንና ጉዳዩ የሚታየው በግልጽ ችሎት እንደመሆኑ ማንኛውም ሚዲያ የመከታተልና የመዘገብ መብት እንዳለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አብራርቷል።
ሆኖም ግን ማንኛውም ሚዲያ የግራ ቀኝ ክርክር በማካተት በሚዛናዊነት የተጠርጣሪን ንፁህ ሆኖ የመገመት መብቱን ጠብቆ ሊዘግብ እንደሚገባ ችሎቱ አሳስቧል።
ፖሊስ በትጋት ምርመራውን አከናውኖ እንዲቀርብ በማሳሰብ ተጨማሪ የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቅዷል።
በታሪክ አዱኛ