የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኢነርጂ መስክ ትልቅ አቅም በመሆን በአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ገቢራዊነት ላይ ሚናው ከፍተኛ ነው – አቶ ደመቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኢነርጂ መስክ ትልቅ አቅም በመሆን በአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጠና ገቢራዊነት ላይ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን የተሳተፉበት የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና አተገባበር ላይ የመከረ ስብሰባ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ተካሂዷል።
ከዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን የተካሄደው የምክክር መርሐ ግብር ነፃ የንግድ ቀጠና አተገባበርን ውጤታማ ለማድረግ እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል፡፡
በውይይቱ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ወደ ተግባር መግባባት የአህጉሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ውህደት የሚያፋጥን መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ትኩረት የተሰጠው የግሉ ዘርፍ በተለይም መድሐኒት አምራቾች፣ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፎችን ለማሳደግ ሊሰሩ በሚገባቸው ሥራዎች ላይ ውይይት መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና አፍሪካን እርስ በርስ በማስተሳሰር ረገድ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እንደ አብነት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በማንሳት በአፍሪካውያን መካከል ትስስርን በመፍጠር እንዲሁም አፍሪካን ከተቀረው ዓለም ጋር በማገናኘት ተጠቃሽ አስተዋፅኦ ማበርከቱን መናገራቸውን የ ሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢነርጂ መስክም ትስስርን በመፍጠር ረገድ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደሚሆን በመግለጽ በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና ገቢራዊነት ላይ የኢትዮጵያን ሚና አቶ ደመቀ አስረድተዋል።
በምክክሩ የሩዋንዳ እና ጋና ፕሬዚደንቶች፣ የቱንዚያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች እና የዓለም አቀፍ ድርጅት ተሳትፈዋል፡፡