የደም ግፊት መለካት ፋይዳዎች
አዲስ አበባ፣ ጥር 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ በርካቶች ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዳላቸው ይነሳል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለባቸው የማያውቁ ናቸውም ይባላል፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት መኖር ደግሞ ለአጣዳፊ የልብ ውጋት ወይም በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ስራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድልን እንሚጨምርም ነው የሚነገረው፡፡
ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ ማናቸው?
• ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ፣ በተለይም ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ፣
• የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ የሆነ፣
• የኩላሊት በሽታ ያለባቸው፣
• የስኳር በሽታ ያለባቸው፣
• የደም ግፊት በሽታ በቤተሰባቸው ታሪክ ያለባቸው፣ ወይም በበሽታው የተጠቃ የቅርብ ዘመድ ካለ፣
• ብዙ ጊዜ የሚጨነቁ፣
• የሰውነት እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ፣
• ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ፣
• የአልኮል መጠጥ የሚያዘወትሩ፣
• ብዙ ጊዜ ጨው የበዛበት ምግብ የሚመገቡ፣
• በቂ ፍራፍሬና አትክልት የማይመገቡ ናቸው፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት ሲኖር የህመም ስሜት ወይም ሌሎች ምልክቶች ላይታዩ (ላይኖሩ) እንደሚችሉም ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
በእዚህም የደም ግፊት መጠን ከፍተኛ ከሆነ እና በጊዜው ህክምና ካልተደረገ ለከፍተኛ የልብ በሽታና በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ስራ መታወክ (ስትሮክ) የመጋለጥ ዕድል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡
ስለዚህ የደም ግፊትዎን መጠን ማወቅ ሕይወትዎን ሊያድን ይችላልና የደም ግፊትዎን በየጊዜው ይለኩ ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ምክር አዘል መረጃውን አጋርቷል ፡፡