Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ግዴታዋን ለመወጣትም ቁርጠኛ ናት – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ግዴታዋን ለመወጣትም ቁርጠኛ ናት ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ልዕለ ሃያል ያልሆኑ፣ሆኖም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ያላቸው ሀገራት መካከለኛ ሃይሎች የሚል መጠሪያ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡

የመካከለኛ ሃይል ሀገራትም በሃያላኖች መገፋፋት እና መሳሳብ የሚፈጠር ዓለም አቀፍ ውጥረት እና ስጋትን በማርገብ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

ዓለም ባለብዙ ዋልታ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ መካከለኛ ሃይሎች በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ጉባዔ ጎን ለጎን ተካሂዷል።

በፓናሉ ላይ አቶ ደመቀ መኮንን ተወያይ ሆነው በመቅረብ ስለኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት ፣ ስለ ዓለም አቀፍ ስርዓት እና የአፍሪካ ሚና ሃሳቦችን አካፍለዋል።

በውይይቱ በዓለም ሰላም ፣ ደህንነት እና ምጣኔ ሃብት ቁልፍ ሚና ካላቸው መካከል አንዷ አፍሪካ እንደሆነች ተናግረዋል።

ድህነት ፣ የቴክኖሎጂ እጥረት ፣ ፋይናንስ ፣ የአየር መዛባት የወለዳቸው ድርቅ እና የአካባቢ መራቆት ዋነኛ የአፍሪካ ተግዳሮቶች ቢሆኑም አህጉሪቱ እድሎቿን በመጠቀም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ የእድገት ሃዲድ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ብሪክስ ፍትሃዊ ዓለም አቀፍ ስርዓት ለመዘርጋት ፣ ቁልፍ የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ እና የኢንቨስትመንት ስበትን ለማሳደግ አዳዲስ እድሎችን ይፈጥራል ነው ያሉት።

እነዚህን የእድገት አቅሞች እና አዲስ የልማት አጋርነትን የሚያስገኝ መሆኑ ኢትዮጵያ ህብረቱን ለመቀላቀሏ ምክንያት እንደሆናት ያነሱት አቶ ደመቀ፥ ይህም የልማት ሥራዎችን በተሻለ አቅም ለመፈፀም እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጥቅም ማግኘት ብቻ ሳይሆን የሚጠበቅባትን ግዴታ ለመወጣት ቀርጠኛ ናት ሲሉ አጽንኦት መስጠታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዓለም በአንድ ሀገር የሃይል የበላይነት የምትመራበት ጊዜ እያከተመ፣ ከአንድ በላይ በሆኑ ሃይሎች ወደ መመራት መሸጋገሯ አፍሪካ በባለብዙ ወገን ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራት ያስችላል ብለዋል።

በዳቮስ ስዊዘርላንድ በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ከአውሮፓ ህብረት ፣ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ከፒተርሰን ኢኒስቲቲዩት እና ከኢንዶኔዢያ የውጭ ፓሊሲ ማህበረሰብ የመጡ ምሁራን ተሳትፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.