Fana: At a Speed of Life!

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ ባሻገር ለማኅበራዊ ትስስር መጎልበት ከፍተኛ ሚና አለው – አፈ ጉባዔ አገኘሁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ ባሻገር ለማኅበራዊ ትስስራችን መጎልበት ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

አፈ ጉባዔው÷ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለከተራና ጥምቀት በዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ተጋምደው አንዱ የሌላው ውበትና ጉልበት እንዲሁም ድምቀትና ሕይወት የሚሆኑበት ነው ብለዋል፡፡

የመልዕክታቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለበዓለ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

«የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ ባሻገር ለማኅበራዊ ትስስራችን መጎልበት ከፍተኛ ሚና ያለው ነው»

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መሀከል አንዱ ጥምቀት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የጥምቀት በዓል ብዝኀ ማንነቶች በኅብር የሚከሰቱባቸው፣ ማንነቶቻቸው ባወረሷቸው ኅብረ ጌጦች የሚያሸበርቁባቸው፣ በቱባ ባህላዊ ትእይንቶቻቸው የሚደምቁባቸው፣ ልሳነ ብዙነቶቻቸውን አጉልተው የሚያወጡባቸው፣ በአጠቃላይ ብዝኀነትን በአንድነት የሚሳዩበት አውድ ነው፡፡

ባህር ተሻግረውና ድንበር አቋርጠው ወደ ሀገራችን የሚመጡ እንግዶችም የመደመማቸው ምሥጢር ኅብራዊነታችን የፈጠረው አንድነታችንንና በአንድነታችን ውስጥ ያለውን ውበት ስለሚመለከቱ ነው፡፡

በጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ተጋምደው አንዱ የሌላው ውበትና ጉልበት፣ ደምቀትና ሕይወት የሚሆኑበት ነው፡፡

ለዚህ ማሳያውም በጥምቀት በዓል ከመዳረሻ ጊዜ ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ በዓሉ በምቾትና በሰላም እንዲጠናቀቅ በተለይ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚያደርጉት ድጋፍና ትብብር ሲታይ «የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር ማኅበራዊ ትስስራችን ለማጎልበት ትልቅ መሠረት ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ መቻቻል፣ መደጋገፍና መተባበር ተጠናክሮ መቀጠል ደግሞ ለሀገራዊ አንድነታችንና ለሕብረብሔራዊ ማንነታችን ትልቅ ዋጋ ያበረክታል፡፡

በኢትዮጵያዊ ነባር ብዝኀ ማንነቶች ላይ የበቀሉ እንደዚህ አይነቶቹ እሴቶች ለዘመናት ሲቀነቀኑ የቆዩ ስሁት ትርክቶችን በማክሰም የወል የሆኑ ትርክቶች ጎልተው እንዲወጡ ለማድረግ፣ ብዝኀ ማንነቶችን አክብሮ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር በአብሮነት ለመኖር፣ ከተነጣይነት አስተሳሰብ ወጥቶ የጋራ ርእይ ለማንበርና ልንደርስበት የምናልመውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳመር ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው፡፡

በመሆኑም ብዝኀ ማንነቶቻችን በማክበርና አንድነታችን በማጠናከር የጋራ ቤታችን የሆነችውን ሀገራችንን ለማልማትና ሰላሟን ለማስጠበቅ ሁላችንም በአንድነትና በመከባበር እንድንቆም በዚሁ አጋጣሚ መልእክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡

በድጋሚ መልካም የጥምቀት በዓል!

አገኘሁ ተሻገር

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.