የከተራና የጥምቀት በዓላት ሲከበሩ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ የከተራና የጥምቀት በዓልን ሲያከብር እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ እንዳሉት÷ በበዓላት ወቅት ከሚያጋጥሙ አደጋዎች መካከል የእሳት አደጋ አንዱ ነው።
በበዓላት ወቅት ከመጠን በላይ ኤሌክትሪክን በመጠቀም በሃይል መጨናነቅና ሻማ ግንባር ቀደም የአደጋ መንስዔዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ኮማሽኑ በዓላትን ታሳቢ በማድረግ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል፤ ከተከሰቱ ደግሞ ፈጥኖ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አመላክተዋል።
ለዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ካሉ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ታቦታቱ በሚያልፉበት አካባቢ የረገቡ የኤሌክትሪክ መስመሮች አለመኖራቸውን በማረጋገጥና ለአደጋ መንስኤ እንዳይሆኑ ባለሙያዎች በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ቅኝት አድርገዋል ብለዋል።
በጥምቀተ ባህር አካባቢዎችም እንዲሁ የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመሮች በሰው ላይ ጉዳት የማያደርሱ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ መሰራቱንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ምእመናኑ በዓሉን በሚያከብሩበት ወቅት በሚያበሯቸው ሻማና ጣፍ ምክንያት አደጋ እንዳይከሰት የበኩላቸውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ከተደረገው ቅድመ ዝግጅት ባለፈ ድንገተኛ አደጋ ቢከሰት ኮሚሽኑ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።
ሕብረተሰቡ በማንኛውም ሰአት አደጋ ተከስቶ ቢመለከት ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችና ለአንቡላንስ አገልግሎት በ939 ወይም በ011-55-53-00 ነፃ የስልክ ጥሪ እንዲያሳውቁ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡