ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑካን ቡድናቸው በዑጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የገለልተኛ ሀገራት ንቅናቄ ርዕሳነ ብሔር እና ርዕሳነ መንግሥታት 19ኛው ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ግንኙነታችንን በይበልጥ ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረናል ብለዋል፡፡
ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር ያለን አጋርነት ለኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ጥረቶች ወሳኝ ነው ሲሉም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር በቀጣናዊ እና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጎንዮሽ ውይይቶቹ በፊት በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግርም÷ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የሕዝብን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ ፈተናዎችን እየተጋፈጡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የባሕር በር የሌላት ኢትዮጵያም ችግሩን ለመፍታት በሰላማዊና በጋራ ተጠቃሚነት መርኅ መሰረት ጥረት እያደረገች መሆኗ አስታውቀዋል፡፡