Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም÷ “ውድ የክርስትና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለጥምቀት በዓል በደህና አደረሳችሁ” ብለዋል፡፡

በሀገራችን በአደባባይ ከሚከበሩት በዓላት አንዱ የሆነው ጥምቀት በድምቀትና በጽኑ መንፈሳዊ ስሜት የሚከበር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ÷ በተባበሩት መንግስታት ትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበ ልንንከባከበው የሚገባ የዓለም ቅርስ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የጋራ ዓላማን ካወቁ፣ ካመኑ ከሚከፋፍላቸው በላይ የሚያስተሳሥራቸው እንደሚበልጥ በተደጋጋሚ አሳይተዋል፤ እያሳዩም ነው በማለት ገልጸዋል፡፡

ጥምቀትን ኢትዮጵያውያንና ከዓለም ዙሪያ ከሚመጡ በርካታ ቱሪስቶች ጋር እንደተለመደው እናክብረው፤ ቅርስነቱን የሚያቆየው የበዓሉ በአግባቡ መከበር ነውና ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

“ፈጣሪ ከሁላችን በላይ የሆነችውን ሀገራችንን አብዝቶ ይባርክልን፤ ሠላምን ያስፍንልን” ሲሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.