በወንጪ-ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም የፈረስ ግልቢያ ውድድርና ትርዒት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በወንጪ-ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም የፈረስ ግልቢያ ውድድር እና ትርዒት ተካሂዷል፡፡
በመርሐ ግብሩ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
አቶ ሽመልስ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷”ዛሬ በደንዲ ሐይቅ ዳርቻ በተካሄደው የፈረስ ግልቢያ ውድድርና ትርዒት ላይ በመገኘቴ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል” ሲሉ ገልጸዋል።
ፈረስ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ልዩ ሥፍራ አለው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ÷ ፈረስ የኦሮሞ ሕዝብ ደስታና ሀዘን ውስጥ፣ በኦሮሞ ሕዝብ ባህልና በዓል ውስጥ ሁሌም አለ ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የኦሮሞም ሆነ የመላው ሕዝብ ታሪክ ከፈረስ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቁመው ÷ ጠላት ሀገርን በወረረ ጊዜ አባቶች በፈረሶቻቸውና ከፈረሶቻቸው ጋር በመሆን የተቃጣባቸውን ጥቃት መመከት እንደቻሉ አውስተዋል።
አባቶቻችን በተለያየ ጊዜና ግንባር የተቀዳጁት ድልም ሆነ የከፈሉት መስዋዕትነት ብቻቸውን ሳይሆን ከፈረሶቻቸው ጋር ነበር፤ ዛሬም ፈረሶቻችን የህዝባችን ጌጦች እና መዝናኛዎች ናቸው ነው ያሉት አቶ ሽመልስ።
እኛ ደግሞ ህዝባችን ለፈረስ ያለውን ክብርና ቦታ በማስቀጠል ፈረሶቻቸውን የኢኮኖሚ ምንጭ ለማድረግ መስራት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንጪ-ዳንዲ ኢኮ ቱሪዝም የተካሄደው የፈረስ ግልቢያ ውድድርና ትርዒት ወንጪ-ደንዲን የሀገር አቀፍና የቀጣናው ትልቁ የፈረስ ጉግስ ውድድር ስፍራ ማድረግ እንደሚቻል ያረጋገጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ሦስቱንም የቱሪስት መስህቦች ማለትም ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሮን በበቂ ሁኔታ የያዘ መሆኑን አስገንዝበዋል
ስለሆነም ሕዝቡ ከዚህ ሃብት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሁሉም አካላት በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡