Fana: At a Speed of Life!

ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፣ ጥር 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን ይፋ አድርጓል፡፡

በሚኒስቴሩ የሥርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ በተያዘው በጀት ዓመት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት በአዲሱ ሥርዓተ-ትምህርት መሠረት እየተተገበረ ነው፡፡

በዚህ መሠረትም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶች ተለይተው የመማር ማስተማር ሒደቱ እየተካሄደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በ2016 ዓ.ም በ2ኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የሚሰጡ የትምህርት ዓይነቶችን መወሰን ማስፈለጉን አስረድተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም በ2016 ዓ.ም ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሁለቱም ዘርፎች ስድስት ስድስት የትምህርት ዓይነቶች እንዲሰጡ መወሰኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ መሰረትም የተፈጥሮ ሣይንስ ተማሪዎች እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ እና ስኮላስቲክ አፕቲቲውድ ቴስት እንዲወስዱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የማህበራዊ ሣይንስ ተማሪዎች እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ኢኮኖሚክስ እና ስኮላስቲክ አፕቲቲውድ ቴስት የሚፈተኑ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

የኢኮኖሚክስ ፈተና ለ2016 ዓ.ም ከ12ኛ ክፍል ብቻ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቁመው ÷ሌሎች የትምህርት ዓይነቶች ከ9 እስከ 11ኛ ክፍሎች በነባሩ ሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም የ12ኛ ክፍል በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮዎችም የፈተና አሰጣጡን በተመለከተ ለተማሪዎች፣ ለወላጆች፣ ለመምህራን እና ለትምህርት ማህበረሰቡ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ከወዲሁ እንዲያሳውቁ አመላክተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.