Fana: At a Speed of Life!

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የአዲጋላ-ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጎበኙ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2016 ( ኤፍ ቢ ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ ( ዶ/ር ኢ/ር) የአዲጋላ-ጅቡቲ ድንበር ተሻጋሪ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ በድሬዳዋ የጅቡቲ ቆንስላ ኃላፊ ሙሴ ሀጂ ጃማ፣ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ፣ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ( ዶ/ር ኢ/ር) እና ሌሎች የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ ፕሮጀክቱን ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ ሃይል የመደገፍ ስራ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ፕሮጀክቱ 28 የከርሰ ምድር ውሃ ማውጫ ጉድጓዶች እንዳሉት እና ከዚህም ውስጥ ግማሹን ወደ ኃይል የማገናኘት ስራ መጠናቀቁንም አመላክተዋል።

በዚህም ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ 20 ጉድጓዶችን ከኃይል የማገናኘት ስራ የሚጠናቀቅ መሆኑን አመላክተው ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በቀን 100 ሺህ ሜትሪክ ኪዩብ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ለጅቡቲ ህዝብ ለመላክ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

በሁለቱም ሀገራት የመጠጥ ውሃ ችግር አለ ያሉት ሚኒስትሩ፥ ችግሮችን የጋራ በማድረግና ሃብትን በመካፈል መሰል ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ፕሮጀክቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በድሬዳዋ የጅቡቲ ቆንስላ ኃላፊ ሙሴ ሀጂ ጃማ፥ ፕሮጀክቱ የበርካታ ዜጎችን የውሃ ፍላጎት እና ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ገልፀው በኢትዮጵያ በኩል በፕሮጀክቱ ላይ ይሰተዋሉ የነበሩ ተግዳራቶች ለመፍታት የታየውን ከፍተኛ መነሳሳት አድንቀዋል።

ፕሮጀክቱን በኤሌክትሪክ ሃይል የመደገፍ ስራው በተፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝም የቆንስላ ፅህፈት ቤት ኃላፊው ገልፀዋል።
ሁለቱ ህዝቦች ሃብቶቻቸውን ተካፍለው በጋራ መልማት በሚችሉባቸው እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ በቀጣይነት በጋራ መስራታቸውን ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የአዲጋላ-ጅቡቲ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በኢትዮጵያና ጅቡቲ መንግስት ትብብር የተገነባ ሲሆን፥ 258 ኪሎሜትሮችን የሚያቋርጥ ድንበር ተሻጋሪ ፕሮጀክት ነው።

በመራዖል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.