በአማራ ክልል የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ለማስቀጠል የጸጥታና የደህንነት አባላት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል-ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2016 ( ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ለማስቀጠል የጸጥታና የደህንነት አባላት በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥና የቀጠናው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ተናገሩ፡፡
በአማራ ክልል ከተለያዩ ዞኖች እንዲሁም ከተማ አስተዳደር ለተወጣጡና በየደረጃው ለሚገኙ የጸጥታና የደህንነት አባላት በጎንደር ከተማ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል።
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የስራ መመሪያ የሠጡት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥና የቀጠናው ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ÷ በአማራ ክልል ፅንፈኛው ኃይል በፈጠረው ሁከትና ግርግር እንዲሁም ዝርፊያና ጦርነት ህዝቡን ለከፋ ችግርና መከራ ዳርጎታል ብለዋል።
ፅንፈኛው ኃይል ላይ በተወሰደው እርምጃ ክልሉን ወደ አንፃራዊ ሠላም መመለስ ተችሏል፤ የተገኘውን አንፃራዊ ሠላም ለማስቀጠል በቁርጠኝነት መስራት ከሠልጣኞቹ ይጠበቃል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ስልጠናው ለክልሉ ሠላም መስፈን የላቀ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙት የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ህብረተሰቡን በታማኝነት ማገልገልና ተልዕኳችሁን በቁርጠኝነት መወጣት ቁልፍ ተግባራችሁ መሆኑን በመገንዘብ ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው÷ የተሰጠው ሥልጠና የሕዝቡን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፤ በመሆኑም ክልሉን ወደ ቀደመ ሠላሙ ለመመለስና ህዝቡን ከደህንነት ስጋት ለመታደግ በትኩረት መሥራት ይገባችኋል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።