የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲ አበባ፣ ጥር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምርትና ምርታማነትን በማሣደግ የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የአፋር ክልል እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአርብቶ አደሮች ቀን በክልል ደረጃ ለ11ኛ ጊዜ በአይሳኢታ ወረዳ ተከብሯል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአፋር ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አሊ መሐመድ በአከባበሩ ላይ እንዳሉት÷ ቀኑ መከበሩ የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማስተዋወቁ ጎን ለጎን አርብቶ አደሩ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡
የክልሉ እንስሳት፣ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኢብራሂም መሐመድ በበኩላቸው÷ ምርትና ምርታማነትን በማሣደግ የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
ለዚህም ፖሊሲዎች፣ የሕግ ማዕቀፎችና የልማት አቅጣጫዎች እየተቀረጹ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም ላላቸው 25 ወረዳዎች፣ 15 የልማት አጋሮችና 42 ሞዴል አርብቶ አደሮች ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡
ከበዓሉ ጎን ለጎንም በአይሳኢታ ወረዳ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል፡፡