ኢትዮጵያ በ3ኛው የደቡብ- ደቡብ ትብብር ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በዑጋንዳ ካምፓላ እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 77 እና የቻይና ሦስተኛው የደቡብ- ደቡብ ትብብር ጉባዔ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡
ጉባዔው በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ዘላቂ ልማት፣ ዓየር ንብረት ለውጥ፣ ድኅነት ቅነሳ እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማሣደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
134 አባል ሀገራትን ባቀፈው የደቡብ-ደቡብ ትብብር ጉባዔ ላይ በአባል ሀገራቱ አብሮነት፣ አንድነት፣ እኩልነት እና የጋራ ቁርጥኝነት ዙሪያ ምክክር እንደሚደረግ መገለጹን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም አሁን ላይ ስላለው የዓለም ሥርዓት እና ውስብስብ የፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ አባል ሀገራቱ የራሳቸውን ዕይታ እና አረዳድ በመድረኩ እንደሚያነሱ ይጠበቃል፡፡