በመዲናዋ ለ1 ሺህ 308 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ1 ሺህ 308 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመን ፈቃድ መስጠቱን የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የእቅድና በጀት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር ወ/ሮ አናትነሽ ታመነ÷ባለፉት 6 ወራት የአልሚዎችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የኢንቨስትመንት ለውጥ ማሻሻያ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል፡፡
በዚህም ለ225 ባለ ሃብቶች የኢንቨስትመንት ለውጥ ማሻሻያ ፈቃድ ለስጠት ታቅዶ ለ121 ባለሃብቶች መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ለ973 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት እድሳት መሰጠቱን ነው ዳይሬክተሯ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
ኮሚሽኑ ለአልሚዎች ከሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች 12 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሰበሰበ ሲሆን፥ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው አገልግሎቶችን በኦንላይን እንዲያገኙ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በዘርፉ 5 ሺህ በላይ ቋሚ እና 3 ሺህ 706 ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደተፈጠረም ወ/ሮ እናትነሽ አብራርተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ