በሚቀጥሉት 10 ቀናት የተለያዩ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ያገኛሉ – ኢንስቲትዩቱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚቀጥሉት አስር አቀናት በሰሜን ምስራቅ ፣በመካከለኛውና የደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ሰሜን ምስራቅ፣በምስራቅ ፣ በምስራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው እርጥበት የበልግ እርሻ እንቅስቃሴን ቀደመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ለእንስሳት የግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም ለሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት ለማሟላት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሚኖረው እርጥበት ለማሳ ዝግጅትና ዘር ለመዝራት የሚጠቅም በመሆኑ አስፈላጊው እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ ኢንስቲትዩቱ ማሳሰቡንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚሁ ወቅት የላይኛውና መካከለኛው ስምጥ ሸለቆ፣ኦሞ ጊቤ፣አፋር ደናክል፣የመካከለኛውና ምስራቃዊ አባይ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣አዋሽ፣ገናሌዳዋ እና ዋቤ ሸበሌ ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡