አንድን ግለሰብ በድንጋይ በመምታት የገደለው ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጣ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ግለሰብ በተኛበት ጭንቅላቱን በድንጋይ ደጋግሞ በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል የተባለው ተከሳሽ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ፡፡
ተከሳሽ አብቹ ቶክቻው መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ስንታሁ ሸሜቦ የተባለው ግለሰብ በተኛበት በድንጋይ ደጋግሞ በመምታት ሕይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ተራ የሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ የመከላከያ ምስክሮችን አቅርቦ እንዲያሰማ ቀጠሮ ቢሰጠውም የመከላከያ ምስክር የለኝም ማለቱን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉም ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠትና የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡