Fana: At a Speed of Life!

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አምስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 503 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

ባለፉት አምስት ወራት በተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ከኅብረተሰቡ 625 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ503 ሚሊየን ብር መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡

ገቢው ከተሰበሰበባቸው መንገዶች ውስጥ÷ ከሀገር ውስጥ የቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከዳያስፖራ ቦንድ ሽያጭና ስጦታ፣ ከፒን ሽያጭ እና 8100ኤ በአጭር የሞባይል የጽሑፍ መልዕክት ይጠቀሳሉ ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር እንዳሉት÷ በገቢ ማሰባሰብ ሂደቱ በክልሎች የሚደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ ወጥ አለመሆን የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ተግዳሮት ሆኗል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የኅብረተሰቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ጥሪ ያስተላለፉት፡፡

በ2016 ዓ.ም ለግድቡ ግንባታ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱም ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.