Fana: At a Speed of Life!

ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የደቡብ-ደቡብ ትብብር አስፈላጊ እየሆነ መጥቷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት የደቡብ-ደቡብ ትብብር አስፈላጊ እየሆነ መምጣቱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሙኤል ኢሳ ተናገሩ፡፡
 
አምባሳደር ሳሙኤል በኡጋንዳ ካምፓላ በተካሄደው የቡድን 77 እና ቻይና ሦስተኛው የደቡብ-ደቡብ ትብብር ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
 
አምባሳደር ሳሙኤል በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግርም÷ የደቡብ-ደቡብ ትብብር ገባዔ ታዳጊ ሀገራት የሚያጋጥሟቸውን ውስብስብ እና ተያያዥነት ያላቸው ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያለውን ጠቀሜታ አስረድተዋል፡፡
 
የቡድኑ የጋራ ድምፅ ተሻጋሪ እና ለትውልድ የሚተርፍ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
 
አሁን ያለው ዓለም አቀፋዊ ቅርፅ አካታችም አሳታፊም ባለመሆኑ መስተካከል እንዳለበትም ማስገንዘባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ኢትዮጵያ በሁሉም የዕድገት መስኮች ያስመዘገበችውን አመርቂ ውጤት በተለይም በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በምግብ እራስን መቻል እና ሀገር አቀፍ የስንዴ ምርት ልማት ላይ የተገኘውን ስኬትም አብራርተዋል፡፡
 
የዓየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድም ስለ አረንጓዴ ዐሻራ ሥራዎችን እና የተገኙ ውጤቶችን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
 
ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ የተተገበሩ ሰፊ የሀገር ውስጥ ማሻሻያዎች ከፍተኛ ዕድገት ያስመዘገቡ የዓለም አቀፍ ደቡብ ሀገር ቀዳሚ ስኬቶች ተደርገው መወሰዳቸውንም አመላክተዋል።
 
ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድን በተመለከተ በሰጡት ገለጻ÷ የባሕር ላይ ሕግን ጨምሮ መሰረታዊ ዓለም አቀፍ ሕጎችን፣ መርሆችን እና ልማዶችን የሚያከብር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
 
ይህ ግልፅ ኢኮኖሚያዊ ስምምነት የሁለቱንም ወገኖች ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ በሰላማዊ መንገድ መተሳሰር፣ መነጋገር እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ሰነዱም አጋርነትን፣ ቀጣናዊ ሰላምና ብልጽግናን የሚያጎለብት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.