ባሕር ኃይል በቀጣይ የሚሠጠውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ለሠራዊታችን ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ኃይል ሆኖ ቀጣይ የሚሠጠውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት ሊወጣ ይገባል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዘመናዊነትን በተከተለ አግባብ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለአምስት ዓመታት የሌሎችን ሀገራት አደረጃጀት ከሀገራችን አካባቢያዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም መዋቅራዊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡
አሁን የተገነባው ባሕር ኃይልም ጠንካራና ብቃት ያለው በየትኛውም የውኃ አካል ላይ ግዳጅ መወጣት የሚችልና በመከላከያ ኃይላችን ላይ ተጨማሪ የማድረግ አቅም የሚፈጠር እንዲሆን ተደርጎ ተገንብቷል ነው ያሉት፡፡
ባሕረኞቹ ከሙያቸው ጋር በቀጥታ ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዓለም አቀፍ ሣይንሳዊ መርሆዎችን፣ የደኅንነት ጉዳዮችን፣ የባሕር ላይ ሕጎችን ተከትለው ሀገር ወዳድ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ ከአመራሮች ይጠበቃል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊት ትስስር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የባሕር ኃይል አመራሮች ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ብሎም ሀገራዊ ሁኔታን ከግምት ያስገባ የሠራዊት ሥነ-ልቦና ግንባታ ላይ ትኩረት በማድረግ ባሕረኞቹ በቀጣይ ለሚሰጣቸው ሀገራዊና ተቋማዊ ግዳጅ በቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አዛዥ ተወካይ ሬር አድሚራል ናስር አባድጋ በበኩላቸው ባሕረኞቹ በአሰሳ፣ በምህንድስና፣ በኤሌክትሪክሲቲ፣ በኮሙኒኬሽንና በትጥቅ ሙያ በሀገር ውስጥና በውጭ መሠልጠናቸውን አብራርተዋል፡፡