Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ትብብር ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገለጸች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከቻይና የንግድ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ልዑኩ በቻይና የዓለም አቀፍ ንግድ ማስፋፊያ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ሊቀመንበር ዣንግ ሻኦጋንግ የተመራ ነው፡፡

በውይይቱ አምባሳደር ምስጋኑ ፥ ለልዑካኑ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።

በቅርቡ በሁለቱ ሀገራት የተደረገውን “የአየር ንብረት ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት” የበለጠ ለማጠናከር ቻይናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በኬሚካልና ማዳበሪያ እንዲሁም በብረታ ብረት ማምረቻ ዘርፎች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ለቻይና ጠቃሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆናለች ያሉት ሚኒስትር ደዔታው ፥ ቻይናም ዋነኛ የኢንቨስትመንት ምንጭና ለኢትዮጵያ ቁልፍ የንግድ አጋር እንደሆነች ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ቀጣናዋን እና የነጻ ንግድ ኢኮኖሚ ዞኖቿን እያሰፋች በመሆኗ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ብዙ እድሎች አሏት ብለዋል ሚኒስትር ዴዔታው።

ኢትዮጵያ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በአፍሪካ ዋነኛ እና ፈር ቀዳጅ መሆኗን ጠቁመው÷ በዘላቂ ልማት፣ በቀጣናዊ ትስስር፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቱሪዝም ዘርፎች ያሉ ዕድሎችን የበለጠ ለመፍጠር ጥረት ታደርጋለች ብለዋል፡፡

ምክትል ሊቀመንበሩ በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያ በቅርቡ የብሪክስ ቤተሰብ በመሆኗ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

በቀጣይ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ዝግጁ መሆኗን መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.