ኢትዮጵያና ቱርክ በወንጀል መከላከል ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስትር ዴዔታ በላይሁን ይርጋ በኢትዮጵያ ከቱርክ አምባሳደር ቤርክ ባራን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷በኢትዮጵያ እና ቱርክ መንግስት በኩል ወንጀልን በመከላከልና በትምህርት ዘርፍ ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቶ በላይሁን ይርጋ÷የኢትዮጵያና ቱርክን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ለማስቀጠልና በተለያዩ ጉዳዮች አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
በተለይም ወንጀልን በመመርመር ሒደት ውስጥ ለዐቃቢያነ ሕግና ለፖሊስ የአቅም መገንቢያ ስልጠናዎችን በመስጠትና ያላቸውን ልምድ በማካፈል የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የሶስት ዓመት የፍትሕ ሪፎርም ሥራ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ ከቱርክ ጋር መስራት መቻል ለዚህ ሥራ መሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ቤርክ ባራን በበኩላቸው÷የተጀመሩ ሥራዎችን አብረው እንደሚሰሩ በመግለጽ በቀጣይም በጋራ ለመስራትና የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የሥራ ሃላፊዎቹ የሀገራቱን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በትብብር እንደሚሰራ መግለጻቸውን የፍትሐ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡