በመዲናዋ የስርቆት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ለሚ ኩራ ክ/ከተማ ተሳፋሪ መስለው በተሽከርካሪዎች ውስጥ በመግባት የስርቆት ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የመሪ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን አማረ ታደሰ እንደገለፁት ÷ ተጠርጣሪዎቹ ጣፎ መስጊድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ታክሲ ተራ ላይ ተሳፋሪ መስለው ሰልፍ ሲጠብቁ ከቆዩ በኋላ ከግለሰብ ኪስ ውስጥ ሞባይል ስልክ ሰርቀው ይሰወራሉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀል ለመፈፀም የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው መረጃ የደረሰው ፖሊስ ክትትል ሲያደርግባቸው እንደቆየም ነው የገለጹት መርማሪው፡፡
በድጋሚ ተሳፋሪዎችን እየጫነ በነበረ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ውስጥም ተሳፋሪ መስለው ለመግባት እየተጋፉ ከተሳፋሪ ኪስ ውስጥ 12 ሺህ 150 ብር ሰርቀው ለማምለጥ ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የታክሲ ሰልፍ ሲጠብቁ ሞባይል ስልክ የተወሰደባቸው ግለሰብ ስልካቸው በተጠርጣሪዎች እጅ መገኘቱን የጠቀሱት ዋና ሳጅን ÷ ገንዘብን ጨምሮ ከመለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ውስጥ ከተሳፋሪዎች ላይ የተሰረቁ ተጨማሪ አራት ሞባይል ስልኮችና የእጅ ሰዓቶችም ተይዘው የምርመራ ስራው መቀጠሉን ጠቅሰዋል፡፡
በተሽከርካሪዎች ውስጥም ሆነ ትራንስፖርት ለመጠበቅ በሚኖር ሰልፍ ላይ የሚያጋጥመውን መገፋፋት እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ለወንጀል ተግባር የሚሰማሩ ግለሰቦች ስለሚኖሩ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባውም ፖሊስ አሳስቧል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በትራንስፖርት መጠበቂያና መናኸሪያ ቦታዎች ላይ በመገኘት መሰል ወንጀሎችን ይፈፅሙ እንደነበርም የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ንብረታቸው የጠፋባቸውና ተጠርጣሪዎቹን ለይተው ለፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃ መሆን የሚፈልጉ መረጃ መስጠት እንደሚችሉም ፖሊስ አስታውቋል፡፡