የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ በግንቦት ወር ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የአክሱም አጼ ዮሐንስ 4ኛ አውሮፕላን ማረፊያ ተጠግኖ በቀጣይ ግንቦት ወር ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንግድ የመሰረተ ልማት ኃላፊ አቶ አብይ ዘነበ ÷ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ደርሶበት የነበረው የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ በ2016 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ጥገናው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ኃላፊው በዛሬው እለት አውሮፕላን ማረፊያውን የጎበኙ ሲሆን ÷ ከፕሮጀክት ሰራተኞች እና ከአክሱም ከተማ ከተውጣጡ የህብረተሰብ ከፍሎች ጋርም ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱም የፕሮጀክቱን ጥገና በ290 ሚሊየን ብር ወጪ ለማከናወን ከንኡድ ኮንስትራክሽን ጋር ውል መፈጸሙም ነው በመድረኩ የተገለጸው፡፡
ጥገናውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችንም በማዘጋጀት ወደ ተግባር እንደተገባ ተጠቅሷል፡፡
በዚህም የዲዛይን ስራዎች ተጠናቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ስራ እንደሚጀመር መገለጹን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡