Fana: At a Speed of Life!

ለሽብር ወንጀል ይውል የነበረ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተያዘ

አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሽብር ወንጀል ይውል የነበረ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ መያዙን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡

እንደ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ2-አ/አ 13092 ተሽከርካሪ መነሻውን አማራ ክልል በማድረግ 106 ኢኮልና የቱርክ ሽጉጦች፣ 26 ሺህ 624 ከመሠል ጥይቶች፣ 60 የክላሽንኮቭ ጥይቶችን ጭኖ አዲስ አበባን አልፎ ቱሉ ዲምቱ የፍተሻ ጣቢያ ላይ በተጠናከረ ክትትልና ፍተሻ መያዝ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ከሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ ጋርም ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ ተመላክቷል፡፡

ፖሊስ በቱሉ ዲምቱ የፍተሻ ጣቢያ የተያዘውን ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ መነሻ በማድረግና ምርመራውን በማስፋት ከፍርድ ቤት የመበርበሪያ ትዕዛዝ አውጥቶ በየካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቤቴል አካባቢ በሚገኙ የተጠርጠሪዎች መኖሪያ ቤት ውስጥ ባደረገው ብርበራ ኮድ 2- አ/አ 67251 Dx ተሽከርካሪ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ እንደጫነ መያዙ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ለወንጀል መፈፀሚያ ይገለገሉበታል ተብሎ የተጠረጠረ ኮድ3-ድሬ 06614 ቶዮታ ተሽከርካሪም መያዙ ታውቋል።

እነዚህ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በአዲስ አበባ እና አካባቢው ላይ የጥፋት ተልዕኮ ለመፈፀም ታስቦ ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ እና ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ በፀረ-ሰላም ኃይሎች እጅ ቢገቡ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችሉ ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በፍተሻ ጣቢያው ከአሁን በፊትም የተለያዩ በርካታ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች የተያዙ መሆኑን የገለፀ ሲሆን÷ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን በመቆጣጠር ረገድ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.