ከ730 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተመላሽ ዜጎች ኑሮ ማሻሻያ ሥራ ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ730 ሚሊየን 804 ሺህ ብር ለተመላሽ ዜጎች የኑሮ ማሻሻያና ጊዜያዊ የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በመንግሥት ጥረት ከመጋቢት 2014 ዓ.ም እስከ መጋቢት 2015 ዓ.ም 133 ሺህ 103 ዜጎች ከሳዑዲ ዓረቢያ መመለሳቸውን በሚኒስቴሩ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ድጋፍና ክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ተግይበሉ ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ታኅሣስ 30 ቀን 2016 ዓ.ም÷ ከሱዳን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመን እና ኦማን 45 ሺህ 875 ዜጎች በመንግሥት ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል ብለዋል፡፡
ተመላሾቹ የሥነ-ልቦና፣ ማኅበራዊ እና ሌሎች አገልግሎቶችን አግኝተው ወደ አካባቢያቸው ማቅናታቸውንም ለፋና ብሮድካስንቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
ወደ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላም ለመሥራት ብቁና ፈቃደኛ የሆኑ ተመላሾች በመረጡት መስክ ስልጠና ወስደው በተለያየ የሥራ መስክ መሠማራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም 40 ሺህ 679 ተመላሾች ስልጠና ወስደው በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት፡፡
ለእነዚህ ተመላሾችም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር 730 ሚሊየን 804 ሺህ 321 ብር ወጪ ተደርጎ ለኑሮ ማሻሻያ እና ጊዜያዊ ቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ መዋሉን አረጋግጠዋል፡፡
በማቋቋም ሥራውም÷ ተመላሽ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ አድራሻቸውን መቀየርና ለድጋፍ ሲፈለጉ አለመገኘት፣ ተመልሰው ወደ ውጭ ለመሄድ መፈለግ፣ በሀገር ውስጥ ሠርተው እንደሚለወጡ ያለማመን የሚሉት ችግሮች ማጋጠማቸውን አብራርተዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው