አቶ ሽመልስ የከተሞችን ዕምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ፖሊሲዎች እየተተገበሩ ነው አሉ
አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተሞችን ዕምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ፖሊሲዎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡
ከተሞቻችንን የምርት፣ የክኅሎትና መልካም አስተዳደር ማዕከል በማድረግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡
በከተሞች የሚስተዋለውን ድህነትና ሥራ አጥነት ለመቅረፍም ከተሞች ያሏቸውን ዕምቅ አቅም ለይቶ ወደ ተጨባጭ ሀብት የሚቀይር ትክክለኛ ፖሊሲ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ነው የገለጹት፡፡
ለአብነትም ከፖሊሲዎቹ መካከል አንዱን የእንስሣት ልማት ዘርፍ ጠቅሰው በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት 15 ሺህ 200 ክላስተሮችን ለመገንባት ታቅዶ መሳካቱን ጠቅሰዋል፡፡
ምንም እንኳን የዕቅዱን መቶ በመቶ መፈጸም ቢቻልም በከተሞች ካለው ድህነት እና ሥራ አጥነት አንጻር እንደ ስኬት የሚቆጠር አይደለም ሲሉ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ በዘርፉ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ለዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ተቀናጅተው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡