ሀገራዊ ምክክር ሁለንተናዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁነኛ መፍትሄ ነው – ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
“ለሀገራዊ ምክክርና መግባባት የምሁራን አበርክቶ” በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያዘጋጁት የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ባለው መድረክ የሁለቱ ተቋማት አመራሮችና ምሁራን የተገኙ ሲሆን÷ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ችግሮቿን እየፈታች ብትመጣም አሁንም ያልተሻገርናቸውና የማያግባቡን በርካታ ጉዳዮችን በምክክርና በውይይት መፍታት ይጠይቀናል ብለዋል።
በዚህም ሀገራዊ ምክክሩ ስኬት በጥቂት ልሂቃን ሳይሆን ምሁራንን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህ ሂደት በተለይም የምሁራን ተሳትፎና እገዛ የላቀ ሚና ያለው በመሆኑ የድርሻቸውን አንዲወጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው÷ምሁራን ለምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ትብብርና ተሳትፏቸውን አንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።