የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔን ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በቅርቡ የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለማስተናገድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴዔታዋ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ÷በቅርቡ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤን እንደምታስተናግድ ገልጸው ፥ ለዚህም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ጉባዔውን እንደተለመደው በስኬት ለማስተናገድ ህብረተሰቡና የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ኢትዮጵያም ሆነ መዲናዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን አስጠብቃ እንድትዘልቅ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
ተቋማት በተለያዩ ንዑስ ኮሚቴዎች ተከፋፍለው ኃላፊነት እንደተሰጧቸውም ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም፥ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሚሊዮኖች የተሳተፉባቸው በዓላት መከናወናቸውን አንስተው ፥ በተለያዩ አካባቢዎች የከተራ፣ የጥምቀትና የቃና ዘገሊላ በዓላት በድምቀት ተከብረዋል ብለዋል፡፡
በዓላቱ ኃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው በየአካበቢው ያለውን ባህላዊ ትውፊት እንደጠበቁ በድምቀት እንዲከበሩ ለማድረግ በርካታ አካላት ትብብር ሲያደርጉ እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡
በዚህም የኃይማኖት አባቶች፣ የጸጥታ ተቋማትና አባላት፣ ወጣቶችና በአጠቃላይ የእምነቱ ተከታዮች እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ የሚገኘው ሕዝብ ከፍተኛ ትብብር ማሳየቱን አውስተዋል፡፡
ለዚህም ሚኒስትር ዴዔታዋ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመሰረት አወቀ