Fana: At a Speed of Life!

የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች ኤክስፖ ነገ ይከፈታል

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የምሥራቅ አፍሪካ አርብቶ አደሮች ኤክስፖ ከነገ ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ዴዔታ እንድርያስ ጌታ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ÷ ኤክስፖው ከጥር 17 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ “አርብቶ አደርነት የምሥራቅ አፍሪካ ኅብረ – ቀለም” በሚል መሪ ሐሳብ ይካሄዳል፡፡

ኤክስፖውን የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በመተባባር ማዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይም ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በኤክስፖው ከኢትዮጵያ በኩል አርብቶ አደሮች የሚገኙባቸው ሰባት ክልሎች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

አርብቶ አደሮችም በኤክስፖው ላይ÷ ባሕላቸውን፣ የቱሪዝም ፀጋዎቻቸውን፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲሁም የተሠሩ የልማት ሥራዎች እንደሚያስተዋውቁ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ኤከስፖው የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ከጎረቤት ሀገራት አርብቶአደሮች ጋር የሚኖራቸውን የልማት ትስስር የሚያጠናክር  እና የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በጋራ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.