አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 እና 251 ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ክስ ተመሰረተባቸው
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 እና 251 ድንጋጌ ተላልፈዋል በሚል ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ክሱ የቀረበባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ሕገመንግስታዊና በሕገመንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው።
በአቡነ ሉቃስ ላይ ሁለት ክሶችን ያቀረበው የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ ነው፡፡
ይህም ተከሳሽ አቡነ ሉቃስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 247 (ሐ) እና አንቀጽ 258(ሀ) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ እንዲሁም የወንጀል ህግ አንቀጽ 251 (ሐ) እና አንቀጽ 258 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል የሚሉ ሁለት ክሶች ናቸው የተመሰረቱባቸው።
በተጨማሪም ተከሳሹ በፀረ ሰላም ሃይሎች የሚፈፀሙ የወንጀል ተግባሮችን ተከትሎ መንግስት ፈፃሚዎቻቸውን ለሕግ ለማቅረብ እና ሕግ ለማስከበር የሚያደርግባቸው ጥረቶችን ለማደናቀፍ እና ህዝብ መንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ ማነሳሳታቸው በክሱ ተመላክቷል።
የክስ ዝርዝሩ የደረሰው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ