ማረሚያ ቤት በሚገኝ ግለሰብ ስም ሀሰተኛ ሊብሬና ከዕግድ ነጻ ሰነዶችን በመጠቀም ገንዘብ ተበድረዋል የተባሉ በሙስና ወንጀል ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማረሚያ ቤት በሚገኝ ግለሰብ ስም ሀሰተኛ የቪ8 ተሽከርካሪ ሊብሬና ከዕግድ ነጻ ሰነዶችን በመጠቀም ገንዘብ ተበድረዋል የተባሉ 4 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ።
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ በወንጀል ተግባር ክስ ተመስርቶበት በማረሚያ ቤት የሚገኘው 1ኛ ተከሳሽ ሱራፌል በቀለ ደግፌ፣ 2ኛ ወ/ሮ ራኬብ መንግስቱ፣ 3ኛ ወ/ሮ ቤተልሄም መንግስቱ እና 4ኛ ወ/ሮ ማህሌት በቀለ ይባላሉ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር 2 (ሀ) እና ንዑስ ቁጥር 3 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።
በዚህም ተከሳሾቹ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ከአ/አ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ከአዲስ ከተማ ቅርጫፍ ጽ/ቤት በማረሚያ ቤት በሚገኝ ሱራፌል በቀለ በሚባል ግለሰብ ስም የተመዘገበ በማስመሰል የቪ8 ተሽከርካሪ ማረጋገጫ ሊብሬና ከዕግድ ነጻ የሚል የተዘጋጁ ሀሰተኛ ሰነዶችን መጠቀማቸው በክስ ዝርዝሩ ላይ ተመላክቷል።
በዚህ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም በ2013 ዓ.ም በፀደቀ የብድር ውል ስምምነት መሰረት ሀርቡ ማይክሮ ፋይናንስ አ/ማ ከሚባል ህዝባዊ ድርጅት በተለያዩ መጠኖች በአጠቃላይ 4 ሚሊየን 575 ሺህ 547 ብር ገንዘብ ተበድረው ጥቅም አግኝተውበት ያልመለሱ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነዶችን መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ዐቃቤ ሕግ ገላጭና አስረጂ ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን የክስ ዝርዝሩ ላይ ጠቅሶ አቅርቧል።
ከአንደኛ ተከሳሽ ውጪ ያሉ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው ክሰ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
አንደኛ ተከሳሽን በሚመለከት ግን ከማረሚያ ቤት አልቀረበም።
ፍርድ ቤቱም አንደኛ ተከሳሽ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ ትዕዛዝ በመስጠት ክሱን ለመመልከት ለጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ