ኢትዮጵያና ሳዑዲ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራ ልዑክ በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡
ልዑኩ ሪያድ ሲደርስ በሳዑዲ ዐረቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት ሚኒስትር ጀነራል ሰኢድ ቢን አብዱላህ አልቃህታኒ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ በሪያድ ቆይታው 911 የመረጃ ማዕከልን ጎብኝቶ ከሌሎች የፀጥታና ደኅንነት የሥራ ሃላፊዎች ጋርም የሁለትዮሽ ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይታቸውም÷በድንበር ደህንነት፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ትኩረት መክረዋል፡፡
በመረጃ ልውውጥና በአቅም ግንባታ ላይም አብሮ ለመስራት መስማማታቸውንም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚሁ ወቅት ጀነራል ሰኢድ ቢን አብዱላህ አልቃህታኒ ÷በሕጋዊ መልኩ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሚገቡ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸውና እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ሀገራቱ በጋራ እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት፡፡
የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ለፖሊሲ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ከሚመለከታቸው የፖሊስ አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉም ተጠቁሟል፡፡