Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኬንያ ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የኬንያ የደኅንነት ተቋማት ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

የኬንያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ኖርዲ ሐጂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኬንያ የመረጃና የደኅንነት ተቋማት በወቅታዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች ምክከር አድርገዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የኢትዮጵያና የኬንያ ወንድማማች ሕዝብ ለዘመናት የዘለቀ የአብሮነት ታሪክ እንዳላቸው አስታውሰዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት አቻ ተቋማትም ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውና ይህንንም አስጠብቀው መዝለቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ተቋማትቱም በመረጃ ልውውጥና በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉትን ትብብር በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ቁርጥኝነት መኖሩን የገለጹት አቶ ተመስገን÷ በዚህም በቀጣናው የሚገኙ ሀገራትን ጥቅም ያማከሉ የአጋርነት ማዕቀፎች የትኩረት ማዕከል እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡

አቻ ተቋማቱ በድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች፣ በአቅም ግንባታ መስኮች፣በሕገወጥ የጦር መሣሪያና የሰዎች ዝውውር ዙሪያ መረጃዎችን በመለዋወጥና የጋራ ኦፕሬሽኖችን በማካሄድ ቀጣናዊ ሰላምንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ መረጃዎችን ከመለዋወጥና የጋራ ኦፕሬሽኖችን ከመምራት ባሻገር ወቅታዊ የሥጋት ምንጮችን በመለየት ተሞክሮዎችን ለመጋራትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት በላቀ ደረጃ እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል፡፡

የኬንያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ኖርዲ ሐጂ በበኩላቸው÷ የሀገራቱ የመረጃና የደኅንነት ተቋማት ሽብርተኝነትንና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የተቀናጀ ስምሪት እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚታዩ የደኅንነት ሥጋቶችን ለመከላከል የሁለቱ ሀገራት ትብብርና ጥምረት ወሳኝ ሚና እንዳለው አውስተዋል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ያላትን ውጤታማ ተሞክሮ እንደ ግብዓት በመውሰድ የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽኖች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

በቀጣናው የሚታዩ የደኅንነት ሥጋቶችን አስቀድሞ በማወቅ ለመከላከል የሚከናወኑ ቅንጅታዊ ሥምሪቶች የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት የመረጃና ደኅንነት ተቋማት የትብብርና የአጋርነት መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም መገለጹን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.