የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ሂደትን ማቀላጠፍ ዓላማው ያደረገ የምክክር መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ሂደትን ማቀላጠፍ ዓላማው ያደረገ የምክክር መድረክ መካሄዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በእንግሊዝ ኤምባሲ አስተባባሪነት በተካሄደው የኢንቨስትመንት የምክክር መድረክ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሐመድ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልእክታቸው እንዳሉትም ÷ የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ዓመታት ፈጣን እድገት እያስመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በፊት ለዘርፉ የሚቀርበው የፋይናንስ ድጋፍ ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰው ፥ መንግስት በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ለዘርፉ የሚለቀቀው የፋይናንስ አቅርቦት ከፍ እንዲል መደረጉንም ነው ያነሱት፡፡
የአምራቾችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ከፍ ለማድረግ ስትራቴጂዎች መዘጋጀታቸውና መሰል አበረታች ሂደቶችም እንዳሉ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ከተጀመረ ጀምሮ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች እንዲሁም ባለሀብቶች ተቀናጅተው መስራት መጀመራቸው ዘርፉን ለማሳደግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
እንግሊዝ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት እና የኔዘርላንድ ኢንተርፕርነር ልማት ባንክ ኤፍ ኤም ኦ እና በዳሸን ባንክ በኩል ግብርና ዘርፉን ለመደገፍ ያበረከቱት አስተዋፅዖ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ በመስራት የተሻለች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ይተጋል ማለታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በምክክር መድረኩ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አመራሮች፣ የእንግሊዝ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተሳትፈዋል።