የአገው ፈረሰኞች ማህበርን 84ኛ በዓል ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገው ፈረሰኞች ማህበርን 84ኛ በዓል ማህበራዊ እሴቱን በጠበቀ አግባብ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ለይኩን ሲሳይ እንደገለጹት÷ የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓል በየዓመቱ ጥር 23 ቀን በተለያየ ዝግጅት ሲከበር ቆይቷል።
በዓሉን ማህበራዊ እሴቱን በጠበቀና የቱሪዝም መስህብ በሚሆን አግባብ በድምቀት ለማክበር ዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም የዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
በዓሉ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች እንደተከናወወ ጠቁመው÷ ማህበሩ የገቢ ማስገኛ ህንፃ እንዲኖረው የሚያስችሉ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የማህበሩ ሊቀመንበር አለቃ ጥላዬ አየነው በበኩላቸው÷ በዓሉን በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን እና ለዚህም አባላቱ ለበዓሉ የሚመጥን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ማህበሩ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና ከቀበሌ እስከ ወረዳ ጠንካራ አደረጃጀት እንዳለው ጠቅሰው÷ በበዓሉ ዕለት ለእንግዶች አቀባበል የፈረስ ትርኢቶች ተዘጋጅተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዕለቱም የፈረሰኛ ዝላይ፣ የስግሪያ ጨዋታ፣ ዳንግላሳ ጉግስና ሽርጥ ፈረስ የተሰኙ ትርኢቶች ለታዳሚው እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።
ማህበሩ ከተመሰረተ 84 ዓመት የሞላው ሲሆን÷ 62 ሺህ 221 አባላት እንዳሉት ተመላክቷል፡፡