Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በበጋ መስኖ 4 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በአትክልትና ፍራፍሬ እየለማ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በበጋ መስኖ 4 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በአትክልትና ፍራፍሬ እየለማ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ተናገሩ።

የቢሮ ሃላፊዋ÷ እስካሁን በተከናወነው ስራ 85 በመቶ በሚሆነው መሬት ላይ ምርታማነትን የማጎልበት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።

በተለይም ዘንድሮ አርሶ አደሩ ሽንኩርትን በኩታ ገጠም በማምረት ከራሱ ፍጆታ አልፎ ገበያን ለማረጋጋት እያዋለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአርሶ አደሩ የተመረተውን ሽንኩርትና ሌሎች የአትክልት ምርቶችን ደግሞ በቀጥታ ለከተማው ነዋሪ በማቅረብ ገበያን የማረጋጋትና የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለአርሶ አደሩ ምርታማነት ማሳደጊያም የማጠራቀሚያ ኩሬ፣ የፕላስቲክ ሸራ ንጣፍ፣ የውሃ መሳቢያ ሞተርና ሌሎች ለበጋ ስራ የሚያገለግሉ ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.