Fana: At a Speed of Life!

የብልጽግና ፓርቲ የተለያዩ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥር 13 እስከ 17 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቀቀ።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ በስብሰባዎቹ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ እንዲሁም ወቅታዊ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን የሚዳስስ ‹ስብራትን መጠገን፣ ለትውልድ መታመን› የሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

የፓርቲው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባቸውን ከጥር 13 እስከ 17 ቀን 2016 በአዲስ አበባ ከተማ አካሂደዋል፡፡

በስብሰባዎቹ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ እንዲሁም ወቅታዊ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን የሚዳስስ ‹ስብራትን መጠገን፣ ለትውልድ መታመን› የሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን በሀገረ መንግሥት ጉዞዋ የገጠሟትን ስብራቶች ዕውቅና መስጠትና እነዚህን ስብራቶች ለመጠገን የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ ሌት ተቀን መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በሰነዱ ላይ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

የዚህም ዋናው ግብ ለዛሬውና ለመጪው ትውልድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጸና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስረከብ ነው፡፡ ለትውልድ መታመን ማለትም ይሄ ነው፡፡

ያለንበት ዘመን ዘመነ መረብ ነው፡፡ በዘመነ መረብ መተሣሠር የግድ ነው፡፡ ዘመነ መረብ በአዎንታ ከተጠቀምንበት የመደመር ጉዟችንን ያሣልጣል፡፡ የመደመር አንዱ ዓላማ ደግሞ ወገን ዘለል ትሥሥሮችን ማበረታታት ነው፡፡ ሀገር የምትገነባውና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሚጸናው በወገን ዘለል ትሥሥሮች ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘመነ መረብ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል፡፡

በተቃራኒው፣ ዘመነ መረብን በአሉታዊ መልኩ ከተጠቀምንበት፣ በተዋንያኑ መብዛትና በአሉታዊ መረጃዎች መስፋፋት የተነሣ ሀገረ መንግሥታችንንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በነጠላ ትርክታቸው የሚገዘግዙ ጠባብ ቡድናዊ ትሥሥሮች እንዲበዙ ያደርጋቸዋል፡፡ እነዚህ ጠባብ ቡድናዊ ትሥሥሮችም በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአካባቢና በጥቅም በመተሣሠር የሚሠሩ ናቸው፡፡ ሀገራቸውን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ለውጭ ጠላቶቻችን አሳልፈው በመሸጥ ለመክበር ይሞክራሉ፡፡ በመሆኑም የዘመነ መረብ ጥቅሞችን በማብዛትና ጉዳቶችን በመቀነስ እነዚህን አፍራሽ ወገኖች መታገል የፓርቲያችን አመራርና አባላት ዋናው ተግባር መሆኑን በስብሰባዎቻችን ወስነናል፡፡

ወገን ዘለል ትሥሥርን በማስፋፋት በማኅበረሰቦች መካከል የተሻለ ሀገራዊ ትሥሥር ለመፍጠር የተሠራውን ሥራ ገምግመናል፡፡ ጠባብ ቡድናዊ ትሥሥሮች በተለያዩ ብሔሮች መካከል ጠላትነት እንዲፈጠር የሠሩት ሤራ እየከሸፈ መሆኑን አይተናል፡፡ ወገን ዘለል ትሥሥርን በማሣለጥ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጸና ሀገር ለመመሥረት የተሠራው ሥራ ፍሬ እያፈራ መሆኑንም ተመልክተናል፡፡ ከዚህ አልፎ ከጎረቤቶቻችን፣ ከአፍሪካ ቀንድና ከዓለም ጋር ያለንን የወገን ዘለል ትሥሥር ሁኔታ ገምግመናል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ ተቀዛቅዞ የነበረው ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያለን ግንኙነት ወደ ቀድሞ ቦታው እየተመለሰ መሆኑን፤ ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያለን ግንኙነትም እየተጠናከረ መምጣቱን አይተናል፡፡

የሀገራችንን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተመለከተ ግምገማዎች ተካሂደዋል፡፡

በአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ዓዕማዶች ማለትም በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እና በአይ.ሲ.ቲ. የተከናወኑ ተግባራት ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡ ጥቅል የኢኮኖሚ ዕድገታችን ባለፈው የበጀት ዓመት 7.2 በመቶ እንደነበር ታይቷል፡፡ ግብርና፣ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ በቅደም ተከተል ለዕድገቱ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውም ተገምግሟል፡፡ የ2016 የበጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገት 7.9 በመቶ እንደሚሆን ተተንብዮአል፡፡ ይሄንንም ለማሳካት አመራሩና አባላቱ ከሕዝቡ ጋር በመሆን በቀሪ ጊዜያት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ተወስኗል፡፡

የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገትና ተደራሽነት፣ የግብርና ምርታማነት፣ የማዳበሪያ ግዥና ሥርጭት፣ የወጪ ንግድ፣ የማዕድን ምርት፣ የስኳር ኢንዱስትሪዎች ጉዳይ በዝርዝር ታይቷል፡፡ በቀጣይ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት አቅጣጫም ተቀምጧል፡፡ ሀገራችን ከፍተኛ ለውጥ ያመጣችባቸው የበጋ ስንዴ ምርት እና አረንጓዴ ዐሻራ በዚህ የበጀት ዓመት ለሚኖራቸው ቀጣይነት ተገቢ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራን በማጠናከርና የዋጋ ንረትን በማቃለል የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የተከናወኑ ተግባራት የተገመገሙ ሲሆን፣ በቀጣይ መወሰድ ባለባቸው ተግባራትም ላይ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡

ሜጋ ፕሮጀክቶች ያሉባቸውን ማነቆዎች በመፍታት እንዲጠናቀቁ እየተደረጉ መሆናቸው ታይቷል፡፡ በቀሪዎቹ ጊዜያትም የተጠናቀቁት እንዲመረቁ፣ ያልተፈቱ ችግሮች ያሉባቸውም ችግሮቻቸው ተፈትተው እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የሕዳሴ ግድቡንም በ2017 የበጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑ ተገልጧል፡፡

የኢኮኖሚ ዕድገቱ ከዚህ በላይ ለመሄድ እንዳይችል አንዱ ዕንቅፋት በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት የተፈጠሩ ትሥሥሮች ያስከተሏቸው አካባቢያዊ ግጭቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ግጭቶች በመፍታት የብልፅግና ጉዞን ይበልጥ ለማፋጠንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ የተሟላ ሀገራዊ ሰላም ለማስፈን እንዲቻል ከታጣቂ ቡድኖች ጋር የተጀመሩ ሰላማዊ አማራጮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን ለሚያቀርቡ አካላት ሰላማዊ መንገዶች እስከሚቻለው ድረስ እንዲመቻቹ፤ ዓላማቸው በነፍጥ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም በሆኑ አካላት ላይ ደግሞ፣ ተገቢው ሕግን የማስከበር ሥራ በተጠናከረ መንገድ እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ኢትዮጵያ እያደገ ከሚሄደው የሕዝብ ብዛቷና ኢኮኖሚዋ ጋር የሚመጣጠን የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ፓርቲው ካስቀመጠው አቅጣጫ በመነሣት፣ የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመዋል፡፡ ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ የኢኮኖሚና የባህል ትሥሥር ያላትን አቋም የሚያሳይ መሆኑ ታይቷል፡፡ በቀጣይም የተጀመረውን የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባራዊ ስምምነት ለማድረስ፣ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራትም ጋር ተጨማሪ የባሕር በር አማራጮችን በሰጥቶ መቀበል መርሕ ለማግኘት ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

ጤናማ ሀገራዊ ትሥሥር እንዲኖር ከሚያስችሉ ጉዳዮች አንዱ የሆነው ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ፣ የሽግግር ፍትሕና የቀድሞ ታጣቂዎች የተሐድሶ ፕሮግራሞች በተገቢው መንገድ ተከናውነው ለውጤት እንዲበቁ፣ ፓርቲያችን መንግሥትን እንደሚመራ ፓርቲ የሚጠበቅበትን ይወጣል፡፡ በፕሪቶርያው ስምምነት የተገኙ የሰላም ፍሬዎችን በመንከባከብ፣ የጎደሉ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሸጋገር ፓርቲያችን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የውስጠ ፓርቲ ትግልን በማጠናከር፣ በብሔራዊነት ላይ የተመሠረተውን ገዥ ሀገራዊ ትርክት በማጽናት፣ የዘመነ መረብን ዕዳ በመቀነስና ምንዳውን በማብዛት፤ ከተለያዩ ወገኖች የሚለቀቁ የሐሰት መረጃዎችን በበቂ ሁኔታ በመመከት፤ ትክክለኛ መረጃ በየደረጃው ለሕዝቡ በመስጠት፤ ለሳይበርና ለዲጂታይዜሽን የሚሆን ሀገራዊ ዐቅም በማሳደግ፤ በአምስቱ የኢኮኖሚ አዕማድ ላይ የጀመርናቸውን የዕድገት መንገዶች በማጠናከር፤ ማህበራዊ ልማትን በማፋጠንና ጥራቱን በማረጋገጥ፣ በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ትሥሥሮች ያስመዘገብናቸውን ድሎች በማስፋት፣ የ2016 የበጀት ዓመትን በውጤት ለማጠናቀቅ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የልማት አጋሮች እና መላው ሕዝብ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ የብልጽግና ፓርቲ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪ ያቀርባል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.