ብልጽግና ፓርቲ ሀገርን ከችግር ለማላቀቅ ፈጠራና ፍጥነት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ እየሰራበት ነው – ወ/ሮ ሙፈሪሃት
አዲስ አበባ፣ ጥር 17፣ 2016 (ኤፍቢ ሲ) ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት በማድረግ ጊዜውን የሚመጥን መፍትሄ መስጠት የሚችሉ አመራሮችና ተቋማትን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሥና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።
ብልጽግና ፓርቲ ለትውልድ ዕዳ ሳይሆን የተሻለ ነገር ለማሻገር እየተጋ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የሥና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አሁን ባለንበት የዘመነ መረብ ወቅት ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩ ሀሳቦች ዕውነት ኮስሳ እንድትታይ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ብልጽግና ይህንን ነባራዊ ሁኔታ በሚገባ የሚረዳ፣ ተራማጅና ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ የያዘ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመተንተን በዕውቀት ላይ የተመሰረተና ጊዜውን የሚመጥን አመራር እያበቃ ይገኛል ብለዋል።
እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን በሚያስተናግድ ዓለም ውስጥ እኩል ለመራመድ ፍጥነትና ፈጠራን መሰረት ያደረገ አካሄድ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት መፍትሄ መስጠት የሚችሉ አመራሮችና ተቋማትን መገንባትን ይጠይቃል ብለዋል።
ዓለም በቴክኖሎጂ መጥቆ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሰላ ጫፍ ላይ መድረሱን ጠቅሰው ለዚህ የሚመጥን የአመራርና የአሰራር ስርአት መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የሚጠይቀውን ብቃት ይዞ ለመገኘት ሁል ጊዜ የሚማርና ወቅቱን የሚመጥን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጁነት እንዳለው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከዘመነ መረብ አኳያ ሲታይ በርካታ መዋቅራዊና ስርአታዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑንም አንስተዋል።
የፖለቲካ ባህላችን ለዴሞክራሲና ለሀሳብ የበላይነት የተመቸ አለመሆኑም ችግሮች እንዲባባሱ በማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ እነዚህን ዕዳዎች ለትውልድ ላለማውረስ ፊት ለፊት በመጋፈጥና ዋጋ በመክፈል ለትውልድ የተሻለ ነገር ለማሻገር እየተጋ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።
መዋቅራዊና ሥርዓታዊ የሆኑ የዋሉና ያደሩ ችግሮችን፣ አዳዲስ ፍላጎቶችን እንዲሁም መጪውን ጊዜና ትውልድ መሰረት ያደረጉ መፍትሄ ተኮር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲው ሀገርን ከገጠማት ውስብስብ ችግር ለማላቀቅ ፈጠራና ፍጥነት ወሳኝ ጉዳይ መሆን በመገንዘብ እየሰራበት ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው በጋራ በመስራት የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም ከግል ፍላጎት ከፍ ብሎ በማሰብና በአስተውሎት በመጓዝ ለጋራ ብልጽግና በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።