በኦሮሚያ ክልል ከቱሪዝም ዘርፍ 25 ቢሊየን ብር ገቢ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ25 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የክልሉ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የእቅድና ክትትል ዳይሬክተር ኦላና ተሾመ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ለጎብኚዎች ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም የሀገር ውስጥ የጉብኝት ባህልን ለማሳደግ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት በደረሰባቸው ቅርሶች ላይ እድሳት እና ጥገና መከናወኑን ጠቁመው÷ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማጠናከር ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በቱሪዝም ገበያ ትንተና መሰረትም ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና ጎብኚዎችን የመሳብ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራትም ከ139 ሺህ በላይ የውጭ እና በርካታ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ሥፍራዎችን እንደጎበኙ ተናግረዋል፡፡
አጠቃላይ ከተለያዩ የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎቶችም ከ25 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አቶ ኦላና ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ